ሀብታሙ ግርማ
መጋቢት 24 ቀን 2012 ዓ.ም
ጅግጅጋ፣ ኢትዮጵያ



አለም በጦር መሳሪያ እሽቅድምድም ሲባዝን ከርሞ፤ የህብረተሰብ ጤና ጉዳይ ተዘንግቶ፤ ይኸው የአለማችን ባለጸጋ ቢልጌትስ ከሶስት አመታት አስቀድሞ እንደተነበየው የጭንቅ ቀን መጥቷል። አሁን አገራት በገፍ ያከማቹትን የጦር መሣሪያ ኮሮና ቫይረስን ለመውጋት ሊጠቀሙበት አልቻሉም፤ አይችሉም። እንዲያው ለሰው ሰራሽ ጦርነት የተዘጋጁበትን ቁራሽ ያህል እንኳ ለህብረተሰብ ጤና ጉዳይ ቢመራመሩበት ኮሮና ዛሬ አይሰለጥንብንም ነበር።

ዛሬ አለም ለዚህ ዝንጉነቷ ዋጋ እየከፈለች ነው።

የአሜሪካ መንግስት ያለፉትን ሃያ አመታት ሲባዝንበት የቆየው የአልቃይዳ መራሹ የ9/11 የሽብርተኝነት ጥቃት የገደለው 2977 አሜሪካዊያንን ነበር። ነገር ግን የናቁት የወረረሽኝ ስጋት ህዝባቸውን እየፈጀ ነው። በአሜሪካን አገር ኮሮና በአንድ ሳምንት ብቻ 3177 ዜጎችን ለህልፈት ዳርጓል።

ይህ የሞት አሃዝ በትንሹ አንድ መቶ ሺህ ሊያሻቅብ እንደሚችል ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከትናንት በስቲያ ለአሜሪካዊያን መርዶ አርድተዋቸዋል።

እንግዲህ የአለም የጦርነት ጋሬጣን በየክፍለ አለሙ የፈጠረች እና እየፈጠረች መሳሪያ በመሸጥ ኢኮኖሚዋን ስታሞቅ ከርማ አሁን ሂሳብ እያወራረደች ነው፥ አሜሪካ። የአለም አገራትም (ኢትዮጵያን ጨምሮ) እንዲሁ ነው።

አሜሪካ የአለም ፖሊስ ናት (ራሷን የሾመች) ሲባል ትርጉሙ ግልጽ ነው። የአሜሪካ ጦስ በሁሉም የአለም ጫፍ አለ ማለት ነው። ይህ ጦሷ ለእኛ ለኢትዮጵያዊያን በበርካታ ጊዜያት የህልውና አደጋን ደቅኖ ኖሯል፤ ከጎሮቤቶቻችን የአፍሪካ እና የአረብ አገራት ጋር በጥርጣሬ እየተያየን ለዘመናት ቆይተናል፤ ባለፉት ሁለት አመታት በጠቅይ ሚኒስትራችን የግል ጥረት ከኤርትራ እና ግብጽን ጨምሮ፣ከበርካታ የአረብ መንግስታት ጋር ወዳጅነት መስርተን ሰላምን ማጣጣም እንደጀመርን አሜሪካ በናይል ወንዝ ውዝግብ የአደራዳሪ ካባ በመልበስ ይኸው የኢትዮጵያን እና የአረብ አገራትን ወደ ዳግም ቁርሾ ካስገባች አንድ ወር እንኳ አልሞላትም።
በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ግን ኮሮና ቫይረስ ገብቶ የማረጋጋት ሥራ ሰርቷል ማለት ይቻላል።

በኢትዮጵያ ላይ ጦር ለማዝመት ላይ ታች ሲሉ የከረሙት የግብጽ የወታደራዊ ፊት አውራሪዎች ባለፉት ሁለት ሳምንታት የኮሮና ወረርሽኝ ገፈት ቀማሾች ሆነዋል፤ ኢትዮጵያ ላይ ያደሙት እና ግልጽ የጦርነት አዋጅ ያስነገሩት የአረብ ሊግ አባል አገራት አሁን በኮሮና ተወጥረው እያቃተቱ ናቸው።

በትራምፕ መሪነት አሜሪካ የአለም የትብብር እና የአብሮነት እሴቶችን አጥፍታ አክራሪ ብሔርተኝነት በመላው አለም ሰፍኖ፤ ሶስተኛው የአለም ጦርነት ፊሽካ መነፋት በስጋት እየጠበቅን ሳለን ግን ኮሮና በድንገት ከተፍ ብሎ የማረጋጋት ስራ እየሰራ ነው።

ቀድሞ የጠላት ያህል ይተያዩ የነበሩ፣ እንደ እስራኤል እና ፍልስጤም ያሉ አገራት እንኳ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ሊተባበሩ ግድ ብሏቸዋል።

ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣም፣ ኮሮና በአገሪቱ ሊከሰት ቋፍ ላይ የነበረውን ብሄር ተኮር የህዝብ ለህዝብ (ሲቪል) ጦርነት እና እልቂት አደጋ ረገብ አድርጎታል። ኮሮና ብሔር ለይቶ አያጠቃም፤ እንሰሳትን እንኳ አያጠቃም።የሚያጠቃው ሰውን ብቻ ነው። በሽታው ከሰው ወደ ሰው በፍጥነት የሚዛመት ስለሆነ ለአንዱ ሰው መዳን ዋስትና የሌላው ሰው ጤነኛ መሆን ነው፤ ስለሆነም አብሮ ለመክረም ካስፈለገ አንድ ሰው ለራሱ ሲል የሌሎች ሰዎችን ጤንነት (ደህንነት) ግድ እንዲሰጠው በሽታው አስገድዶታል።

በመሆኑም ቢያንስ ኮሮና ቫይረስ በአገሪቱ እስካለ ድረስ በኢትዮጵያ ሰው የሚፈላለገው በብሔሩ ሳይሆን በሰውነት መስፈርት ብቻ ነው። እናም የኮሮና ወረርሽኝ መተባበር፣ መተሳሰብ እና አንድነትን በግድም ቢሆን አምጥቷል።

የእኛ ጥንቃቄ ፣ እንዲሁም የፈጣሪ ቸርነት ታክሎበት ከመጣብን መቅሰፍት እንደምንወጣ እምነት አለኝ። ታዲያ በጭንቅ ወቅት ያገኘነው የአንድነት መንፈስ በሰላሙም ጊዜ ይቀጥል ይሆን? ለሁሉም ጊዜ መልስ አለው!


Discover more from Habtamu Girma Demiessie (ሀብታሙ ግርማ ደምሴ)

Subscribe to get the latest posts to your email.

Published by Habtamu Girma Demiessie (ሀብታሙ ግርማ ደምሴ)

Habtamu Girma Demiessie is assistant professor of Economics at Jigjiga University, Ethiopia. An academic and a writer, Mr. Habtamu authored 8 books and published more than 85 scholarly works. His academic & literary works, which can be categorized as original research article, commentary, opinion or view point pieces, appeared on well read journals, Newsletters, print media and/or social media outlets in Ethiopia and abroad Readers interested to throw comments and/or critics on his works may contact the author via the following addresses: E-mail: • ruhe215@gmail.com • hab200517@yahoo.com Telephone (Mob): • +251 (0) 912 064 095. Website/Blog sites: •https://www.jigjigauniversity.academia.edu/HabtamuGirma •https://www.ruhehabtamu.wordpress.com/HabtamuGirma •https://www.researchgate.net/profile/Habtamu_Demiessie2

አስተያየት ያስቀምጡ

ይህ ጣቢያ አይፈለጌ መልዕክትን ለመቀነስ Akismet ይጠቀማል። የአስተያየትዎ ውሂብ እንዴት እንደሚሰናዳ ይወቁ

Discover more from Habtamu Girma Demiessie (ሀብታሙ ግርማ ደምሴ)

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading

Design a site like this with WordPress.com
ጀምር