ከአምስቱ የፋሺስት ወረራ ዓመታት ምን እንማራለን?

ከታሪክ ማህደር እንደምንረዳው የአምስቱ አመታት የፋሺስት ጣልያን ወረራ (1936-1941 ዓ.ም) የተሳካው በውስጥ ድክመታችን የተነሳ ነው፡፡ እንደ ህዝብ፣ እንደ መንግስት የምንወስደው ሃላፊነት አለብን:: ኢተዮጵያዊያን ለዘመናት የኖርነው የህይወት ዘይቤና ፍልስፍና ስራን የሚያበረታታ አለመሆኑና ህዝቡ ለቁሳዊ ሀብት ያለው ግምት ዝቅተኛ መሆን ኢትዮጵያን ከሌላው ዓለም በኢኮኖሚ በእጅጉ ወደ ኋላ አስቀርቷታል፡፡ በእርግጥ በተለያዩ የዘመን ማዕቀፎች ኢትዮጵያን ያስተዳደሩ አብዛኞቹ መሪዎች ህዝቡ ይህን አስተሳሰብ እንዲያዳብር አይፈልጉ እንደነበር ተደጋግሞ ቢጻፍም ህዝቡ ከተወቃሽነት አይድንም፥ መሪዎች ህዝቡን መስላሉ የሚለውን መርሳት የለብንም::

የሆነው ሆኖ የኢጣሊያ ጦር ዘመናዊ መሳሪያ ታጥቆ፣ በምድርና በአየር በወገን ጦር ላይ መዓቱን ሲያወርድ፣ኢትዮጵያዊያን አርበኞች ግን ከሃምሳ አመታት ቀደም ብሎ በአድዋ ጦርነት ታጥቀው የዘመቱትን ባህላዊ መሳሪያዎች ነበር የታጠቁት፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን እንዲህ ጽፈዋል፡-
ኢትዮጵያ ያለችበትን በጣም ዝቅተኛና ቆሞ ቀር ደረጃ በተግባር አስመሰከረች፤ይህ አዲስ ዕውነት የኢትዮጵያ ህዝብ ለዘመናት የነበረውን አልበገር ባይነት ከነኩራቱና ክብሩ ገፈፈው፤ የመንፈስ ሃይሉ ደቀቀ፤ አንገቱን ደፋ፡፡

ለማይጨው ጦርነት መሸነፍ ሌላው ሰበብ፣ ጦሩን ያዘመቱና የመሩ ሹማምንት ከልባቸው አልነበሩም፣ ወኔ የከዳቸው ነበሩ የሚሉ መረጃዎች አሉ:: የዚህ ምክንያት ደግሞ የዘመኑ የኢትዮጵያ ፖለቲካና የአስተዳደር ስርዓት ለአገራዊ መግባባት በዝቅተኛ ደረጃ እንኳ እውቅና ያልሰጠ፣ ፍትህና መልካም አስተዳደር የማያውቅ፣ ደካማ መሆኑ ነበር::
የአሁኑ የኢትዮጵያ ገዢዎች ከዚህ መማር ያለባቸው ቁም ነገር ቢኖር፣ የሚከተሉትን የፖለቲካ ስርዓት መለስ ብለው መቃኘት እንደሚገባቸው ነው:: አስተዳደራቸውና ፖሊሲዎቻቸው በተለያየ ደረጃና ስልጣን ያሉ የመንግስት አካላትን የማይከፋፍል፣ የህዝብና መንግስትን ግንኙነት የማያሻክር መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋቸዋል::
ይህ ካልሆነ ግን ውስጣችንን አድክሞ የኢትዮጵያና ህዝቦቿን ሰላምና ብልጽግናን ለማይሹ የውጭ ሀይሎች ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፥ የአገርና የህዝብ ህልውናም በእጅጉ አደጋ ላይ እንደሚወድቅ፣ ለራሳቸው ለፖለቲካው አራማጆችና (ገዥዎች) ጭምር የማይበጅ መሆኑን ከአጼ ሀይለ ስላሴና ባለሟሎቻቸው ስደትና የመንግስታቸው መፍረስ ሊማሩ ይገባል::

Design a site like this with WordPress.com
ጀምር