ሀብታሙ ግርማ፤ መጋቢት 13 ቀን 2012 ዓ.ም፤ ጅግጅጋ፣ ኢትዮጵያ

የኮሮና ቫይረስ ኢትዮጵያ ገባ ከተባለ አስር ቀናት አለፉ፤ በእነዚህ ቀናት በስራ ምክንያት በተዘዋወርኩባቸው ድሬዳዋ፣ ሐረር እና ጅግጅጋ ከተሞች ህዝቡ ስለ በሽታው ያለውን አመለካከት ለመታዘብ እድሉ ነበረኝ፡፡ አብዛኛው ህዝብ የሚለው በሽታው ከጸሎት በቀር ምድራዊ በሆነ ነገር መጠንቀቅ አይቻልም ነው፤ ስለሆነም የፈጣሪ ቁጣ ነው፡፡ ለአንዳንዶቹ ደግሞ ከበሽታው ማምለጥ የማይቻልበት ምክንያት በአብዛኛው ህዝብ የቀን ገቢ ያለው በመሆኑ ኢኮኖሚያችን አንድ ቀን እንኳ ቤት እንድንውል አይፈቅድም የሚል ነው፡፡ ኢትዮጵያ የአምላክ የቃልኪዳን አገር ስለሆነች በሽታው እኛን አይመለከተንም የሚሉም በርካታ ናቸው።

በእኔ እምነት ሁሉም ፍጥረት፣ ሰውም ሆነ እንሰሳ፤ ኢትዮጵያዊም ሆነ የሌላው አገር ዜጋ ሁሉ የፈጣሪ ልጆች ናቸው፡፡ ፈጣሪ በሽታን ለአንድ ህዝብ ሰጥቶ ለሌላው አይከለክልም፡፡ በእስልምናም ሆነ በክርስትና እምነት አስተምህሮች መሰረት የሰው ልጅ በህገ-ልቦናው (free will) ይኖር ዘንድ ይገደዳል፡፡ ሰው ሁሉ በህሊናው እና በአእምሮው ተመርቶ ክፉና ደጉን እንዲለይ፣ የህይወት ምርጫውንም ሃላፊነት ወስዶ እንዲንቀሳቀስ ሃይማኖቶች ያስተምራሉ፡፡ በመሆኑም ነፍስ ያወቀ ሰው ሁሉ የእለት ተግባራቱን የሚኖረው በምርጫው እንደመሆኑ ድርጊቶቹ ለሚያመጡት ውጤቶችም ሃላፊነት ይወስዳል፡፡

በሽታውን የፈጣሪ ቁጣ አድርጎ በተስፋ መቁረጥ እጅ አጣጥፎ መጠበቁ አግባብ አይደለም፡፡ስለሆነም ወደ ፈጣሪ እጅን መዘርጋቱ መሰረታዊ መሆኑ ሳይዘነጋ፣ ነገር ግን አእምሯችንን መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ሁላችንም እንደየእምነታችን ጸሎት ማድረጉ ወሳኝ እንደሆነ አምናለሁ፤ ነገር ግን በህክምና ባለሙያዎች የሚሰጡ ምክሮችን ቸል ብሎ ጸሎት ማድረጉ አንዱን ይዞ አንዱን ጥሎ አይነት ነው፡፡

ከህዝቡ ከሚነሱ ጉዳዮች አንዱ የሆነው ደካማ ኢኮኖሚያችን ለቫይረሱ ስርጭት የራሱ አስተዋጽኦ ሊኖረው የሚችልበት እድል ሰፊ የመሆኑን ጉዳይ እኔም የምቀበለው ነው፡፡ ቀደም ብሎ እደተጠቀሰው ኢትዮጵያዊያን እንደ ቤተሰብም ሆነ እንደ አገር የእለት ኑሮ ነው ያለን። ስራችንን ትተን በቤት መቀመጡ አይቻልም። አገሪቱ ያላት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለአስራ አምስት ቀናት እንኳ አይበቃም፤ እያንዳንዱ ኢትዮጵዊ ከዕለት ጉርስ ያለፈ ለክፉ ቀን የሚመነዝረው ተቀማጭ ገንዘብ የለውም፡፡ በመሆኑም ከስራው ተስተጓጉሎ ቤቱ ተቀምጦ ሊውል አይችልም፤ አለበለዚያ ከኮሮና በላይ በረሃብ ማለቅ ነው የሚሆነው፡፡ ነገር ግን አያደድርስና በሽታው ከቁጥጥር ውጭ ከሆነ ሰው ቤቱ እዲቆይ ሊገደድ የሚችልበት አጋጣሚ ይኖራል፡፡ በዚህ ወቅት ኢኮኖሚ የሚባል ነገር ጉዳይ አይሆንም፤ በዚህ አስከፊ ወቅት አስታማሚ ቀርቶ ቀባሪም እንደማይኖር ከሰሞኑ የጣሊያን ተሞክሮ መማር ይገባል፡፡
ጣሊያን በአለም ምርጥ የህብረተሰብ የጤና ስርዓት ከዘረጉ አገራት ቀዳሚዋ አገር ናት፡፡ አገሪቱ ለዜጎቻ ለዜጎቿ ተደራሽ ባደረገችው አስተማማኝ የስርዓተ ምግብ ዝግጅቷ ትታወቃለች፡፡

ታዲያ ኮሮና እንዴት ይህችን አገር እንዲያ በጥቂት ሳምንታት ሊያፍረከርካት ቻለ?

የዚህ መልሱ ለኢትዮጵያዊያን የማስጠንቀቂያ ደውል ነው።

ከተለያዩ የሚዲያ ምንጮች እንደተረዳሁት ኮሮና በጣሊያን ከባድ እልቂት ያስከተለው ህዝቡ ስለ በሽታው የተዛባ አመለካከት ስለነበረው ነው።ዛሬ በሽታው ከአገሪቱ ከቁጥጥር ውጭ ሊሆን የቻለው በህዝቡ ቸልተኝነት እንደሆነ በጣሊያን የሚኖር የቅርብ ጋደኛዬም ነግሮኛል።

ይህ መልዕክት በጣሊያን አገር ከሚኖር ኢትዮጵያዊ ለወገኖቹ የሰደደው የ ‘እባካችሁ ተጠንቀቁ ተማጽኖ ነው። ስንቶቻችን ለተማጽኖው ልባችንን ከፍተናል?

በጣሊያን ኮሮና ከገባ ወራት ቢቆጠርም ህዝቡ የተለመደ አይነት የኑሮ ዘይቤን ተከትሎ በመቆየቱ በሽታው ስር ሰዶ ቆይቷል። በሽታው በባህሪው ለአስራ አራት ቀናት ራሱን ደብቆ ስለሚያቆይና በምርመራም ቶሎ ስለማይታወቅ ዛሬ ጣሊያንን ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በኋላ የታየ የሞት መዓት አውርዶባታል፡፡ አገሪቱ የተዳከመውን ኢኮኖሚዋ በበሽታው እንዳይጎዳ በማሰብ በሽታው አስከፊ ደረጃ ሳይደርስ ለመቆጣጠር አልቻለችም፡፡ የአገሪቱ ዜጎችም ኢኮኖሚ ጫና ስላለባቸው የተለመደ ስራቸውን ማከናወናቸውን አላቆሙም።

በእርግጥ በእኛው አገርም እንዲሁ ከስራ ቤት መዋል ጫናው ከባድ እንደሆነ እኔም የምኖረው በመሆኑ አይጠፋኝም፡፡ ነገር ግን በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት እንደመኖራችን የኑሮ ዘይቤያችንን ማስተካከል አለብን፡፡ ይህን ማድረጋችን መጠነኛ የኢኮኖሚ ጫና ሊያሳድርብን ቢችልም ሙሉ ለሙሉ ከስራችን አያስተጓጉለንም፤ አብዛኛው እንዲያውም ጥንቃቄ ከማድረግ ጋር እንጂ ከኢኮኖሚ ጋር አይያያዝም፡፡

በሽታው አስከፊ ደረጃ ከመድረሱ በፊት ለመቆጣጠር ይቻል ዘንድ የኑሯችን መርህ መቃኘት ያለበት በሶስቱ የመ-ህጎች፦ መጸለይ፣መታጠብ፣ መራራቅ መሆን አለበት፡፡

ኢትዮጵያዊያን ይህንን ማድረጋችን ምንም ኢኮኖሚያዊም ሆነ ሌላ ወጪ የለውም፡፡

የኮሮና ወረርሽኝን ስርጭት ለመግታት ከእንዳንዳችን የሚጠበቀው አስተውሎት እና ጥንቃቄ ብቻ ነው!


Discover more from Habtamu Girma Demiessie (ሀብታሙ ግርማ ደምሴ)

Subscribe to get the latest posts to your email.

Published by Habtamu Girma Demiessie (ሀብታሙ ግርማ ደምሴ)

Habtamu Girma Demiessie is assistant professor of Economics at Jigjiga University, Ethiopia. An academic and a writer, Mr. Habtamu authored 8 books and published more than 85 scholarly works. His academic & literary works, which can be categorized as original research article, commentary, opinion or view point pieces, appeared on well read journals, Newsletters, print media and/or social media outlets in Ethiopia and abroad Readers interested to throw comments and/or critics on his works may contact the author via the following addresses: E-mail: • ruhe215@gmail.com • hab200517@yahoo.com Telephone (Mob): • +251 (0) 912 064 095. Website/Blog sites: •https://www.jigjigauniversity.academia.edu/HabtamuGirma •https://www.ruhehabtamu.wordpress.com/HabtamuGirma •https://www.researchgate.net/profile/Habtamu_Demiessie2

አስተያየት ያስቀምጡ

ይህ ጣቢያ አይፈለጌ መልዕክትን ለመቀነስ Akismet ይጠቀማል። የአስተያየትዎ ውሂብ እንዴት እንደሚሰናዳ ይወቁ

Discover more from Habtamu Girma Demiessie (ሀብታሙ ግርማ ደምሴ)

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading

Design a site like this with WordPress.com
ጀምር